Blog

Written By Negussie Bulcha

               ኀይላት የሚፎካከሩብ ዘመን፤ “እስቲ አሳየኝ ላሳይህ” ጫፌን ንካና ወዮልህ”፡፡ በፖለቲካው አደባባይ፣ በጦሩ ዐውድማ፣ በምርምሩ ጓዳ፣ በሸቀጡ ገበያ ልካቸው እየታየ፣ የጉልበታቸው ጫና እየተፈተሸ ነው፡፡ አንዳንዶቹ የተባለላቸውን ያህል ብርቱዎች እንዳልሆኑ ይፋ እየወጣ፣ ሲኮፈስ ሲከሸን የነበረው ገበናቸው እየተገለጠ “ይኸው ነው እንዴ?” እየተባለ ነው፡፡ ዕምቅ ኀይላት ልቅ ኀይላት እየሆኑ ነው፡፡ ውስጥ ውስጡን ሲብላላ የኖረ፣ ሲጠራቀም የቆየ ጉልበት ለተኩስ ያሞጠሞጠ አፉ ድንገት እየፈነዳ ነው፡፡ በየቦታው የኀይል ርችት ይሰማል፡፡ ዐየሩን ጢስ ሞልቶታል፡፡ ያለንበትን ዐለም እየናጠ ያለው አብዛኛው ኀይል የጥፋት ነው፡፡ ሰው ገዳይ፣ ንብረት አውዳሚ፣ ጤና ሰላቢ፣ ፍርሃት ጫሪ፣ ጠብ አቀጣጣይ፣ ሀሰት አራማጅ፣ ጨለማ አስፋኝ፣ እውነትን አፋኝ ኀይል ነው፡፡ በዚህ የኀይል ፉክክርና የኀይል ክስተት የሕያው እግዚአብሔር ቤተክርስቲያን የት ቦታ ቆማለች? ኀያል ናት ኀይል አልባ? የጦር ሠራዊት ናት ወይስ የትርኢት ታዳሚ? የኀይል ያላት እንደሆነ የኀይሏ ምንጭ ምንድን ነው? ክምር የአስተሳሰብ ገለባ በመናድ እንጀምር፡- የቤተክርስቲያን እውነተኛ ኃይል የአባሎቿ ቁጥር አይደለም፡፡ “ወገኖቼ” የምንላቸው ሲከማቹ የልብ ልብ ቢሰማን ተፈጥሮአዊ ነው፡፡ በያለንበት ዘራችን ቢበራከት እንዴት ጥሩ ነው ግን በእጁ አንድ የጦር መሳሪያ ያልያዘ ወይም “ጥይት በሌለበት አሮጌ መዘውር” የሚያቅራራ የሕዝብ ጥርቅም ቢሆንስ? ቁጥር ብቻውን ኀይል ይኖረው እንደሆነ የድምጽ ብቻ ኀይል እንጂ መንፈሳዊ ኀይል አይደለም፡፡ ሕዝባዊ ጥንካሬ እንጂ መለኮታዊ ጉልበት አይደለም፡፡ በኅብረት ድምጽ ማሰማት፣ በኅብረተሰብ ደንቦችና ውሳኔዎች አዎንታዊ ተፅዕኖ ማምጣት ጠቃሚ ቢሆንም የክርስቶስ አካል ውስጣዊ ኃይል መገለጫ አይደለም፡፡ እያንዳንዱ ግለሰብ በተፈጥሮ የያዛቸው ወይም ቆይቶ በልምድና በትምህርት ያዳበራቸው ችሎታዎች፣ ዕምቅ ኀይሎች፣ ምን እንደሆኑ ተገንዝቦ ለጥቅም የሚውሉበትን መፈለግ ጥሩ መጋቢነት ነው፡፡ መኖሩ ያልታወቀ፣ ቢታወቅም ያልዳበረ ስንት ዐቅም በየሰዉ ውስጥ ተጠራቅሟል! ይሁን እንጂ የቤተክርስቲያን የኀይል ጥማት የሚረካው በሰው ችሎታ አውጫጪኝ አይደለም፡፡ አዳዲስ ስሞች ለአሮጌ ሰዎች ብንሰጥ ኀይል አይመጣም፡፡ የስሞች ገናናነት-ቤተክርስቲያናዊ ይሁኑ ነገረ መለኮታዊ – ሰዎችን ልዩ አያደርጋቸውም፡፡ ለምሳሌ ወንጌላዊውን ፓስተር፣ ፓስተሩን ሊቀጳጳስ ብንለው በነፍሱ ውስጥ የኀይል ቅመም መጨመራችን አይደለም (የቤተክርስቲያን አገልጋዮች እንደየስጦታቸውና እንደ አገልግሎታቸው ቢሰየሙ አልቃወምም)፡፡ አንዳንድ አሰያየሞች ልዩ ትንግርት እንደሚሠሩ ዐይነት ለማዕረግና ለስያሜ የሚጨነቁ፣ የቤተክርስቲያንንም የኀይል እጦት ከዚህ ጋር የሚያያይዙ የኀይል ምንጭ ምን እንደሆነ የዘነጉ ሰዎች ይመስሉኛል፡፡ ቤተክርስቲያን ኀይል የተወሰኑ ሰዎች ወይም ልዩ ቡድኖች ወይም ቢሮዎች እንደሆኑ መቁጠርም ከአሰያየሙ አመለካከት ብዙ ፈቀቅ አይልም፡፡ አዲስ ኪዳናዊ የኀይል ክስተት በአንዳንድ ግለሰቦችና ቡድኖች ሳይሆን “ሁሉን በሁሉ በሚሠራ” በእግዚአብሔር አደላዳይነት በክርስቶስ መላ አካል ውስጥ የሚገለጥ ነው፡፡ የምናሞግሰው ትውልድ አሮጌም ይሁን አዲስ፣ የቤተክርስቲያን ኀይል የአንድ ልዩ ትውልድ ድርሻ እንደሆነ ማሰብ ደግሞ የእግዘአብሔርን ሕዝብ ጠቅላላ ታሪክ ከሚያጣጥል፣ በቀለመ መነፅር ከሚያይ ማንነት የሚወጣ ድፍረት ይመስለኛል፡፡ “ወየው ሙሴ ሞተ! በፈርኦን ፊት በጽናት የቆመ፣ ያ ጀግና ነቢይ የግብፅን ጠንቋዮች አፍ ያዘጋ ÷ ወየው ሙሴ ሞተ፡፡ ያን የተኛ ዘንዶ ቀይ ባሕርን ለሁለት የቆረጠ በዚያ አስፈሪ ምድረ በዳ በታላቅ ጥበብና ትዕግሥት ሕዝቡን የመራ ወየው ወየው ሙሴ ሞተ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ጅብ በላው” የሚሉ ታሪክ አስታዋሾች፣ እግዚአብሔር ረሾች የያዙት ግማሽ እውነት ነው፡፡ ሙሴን በባሕር ከመጣል ያዳነ፣ በግብፅ ቤተ መንግሥት ያሰለጠነ፣ በበግ ጥበቃ ልቡን የገራ፣ በሰማያዊ ጥሪ ወደ ሥራ ያሠማራ፣ በተቃውሞ ፊት ግንባሩን እንደ ድንጋይ ያጠነከረ፣ በእጁ ታምራት የሠራ ማን ሆነና! ዛሬ አዲስ ታሪክ ሊሠራ አይችል? ሙሴ ቢሞት እግዚአብሔር ሞቷል እንዴ! ፈቀቅ ብለን ብንቃኝም ተመሳሳይ ወልገዳነት በሌላው ጎራ ይገኛል “ኢያሱ ተነሣ የትውልዱን ጥሪ ይዞ፣ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መንገድ፣ ተገልጦ ባልተሰማ ጉልበት፣ ከሌሎች ጋር በማይጋራው ልዩ አሠራር፡፡ ማንንም ረዳት አይሻም፣ ታሪክን ለባለ ታሪኮች ወርውሮ፣ ጋሻ ጦሩን ይዞ ይዝመት አዲሱ የኢያሱ ትውልድ ሙሴዎቹን እየረሳ፣ አዲስ ባሕል እየመሠረተ ይገስግስ፣ አደናቃፊዎቹንና አሮጌዎቹን ልክ ልካቸውን እየነገረ፣ አዲሱን ትውልድ በጥቅል እያከበረ ወደፊት ይሩጥ ሰው ሁሉ ያለ ፍሬ የቀረውን ሙሴን ትቶ ኢያሱን ይከተል” ይህ ምን ይባላል? ሸውራራ ነገር መለኮት ይባላል፤ ስስታም ርዕዮት፡፡ እግዚአብሔር ሥራ የጀመረው ዛሬ ነው እንዴ! “ከሙሴ ጋ እንደሆንሁ” ማለት ምን ማለት ነው? አዲስ አምላክ አይደለሁም ማለት ኮ ነው፡፡ “ለአባቶቻቸው የማልኩላቸውን ርስት ታወርሳለህ” ማለትስ ምን ማለት ነው? መመሪያ አልተለወጠም ማለት እኮ ነው፡፡ የተያያዘውን የእግዚአብሔርን ታሪክ ለምን እንበጣጥሰዋለን? እንግዲህ የነገሩ ማሠሪያ ምንድን ነው ቢሉ፡- ኀይል የተቋጠረው በአንድ የተለየ ትውልድ ውስጥ ብቻ ነው የሚለው አመለካከት መጽሐፍ ቅዱሳዊም ጠቃሚም አይደለም ለማለት ነው፡፡ የቤተክርስቲያን ኀይል የፖለቲካ ጉልበት ካልሆነ፣ የስያሜ ርችት ካልሆነ፣ አሮጌው ትውልድ ካልሆነ፣ አዲሱም ትውልድ ካልሆነ፣ የጩኸታችን ብዛት ካልሀነ፣ የክርክር እሳት ካልሆነ፣…..እንግዲያውስ ምንድነው? ከሁሉ በላይና በፊት የቤተ ክርስቲያን ዕምቅ ኀይል ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ አባቱ ከሞት ሲያስነሳውና በቀኙ ሲያስቀምጠው የታየው ከተፈጥሮ ሕግጋት በላይ የሆነ ብቻ ሳይሆን ከዲያቢሎስና ከጭፍራው ዐድማ ሁሉ በላይ የሆነ መለኮስ የኀይል ክስተት ነው፡፡ይኸውም ኀይል ኢየሱስን የጌቶች ጌታ፣ የአለቆች አለቃ፣ የገዥዎች ገዢና የስልጣናት ሁሉ ስልጣን አድርጎ አገነነው፡፡ በሚታየውም በማይታየውም ዓለም ውስጥ፣ አሁን ባለውም በሚጣውም ዘመን ውስጥ፣ ወደር እንዳይገኝለት አርጎ ስሙን አላቀው፡፡ ይኽ ሁሉ የሚያስደስተንና የሚያስገርመን እየሆነ ሳለ እኛን በሚመለከት በለይ ቅርብ ደስታና ነፍሳዊ አለኝታ የሚሰጠን ይህ ባለ ወደር የለሽ ኀይል ጌታ የእኛ አለቃና አሳዳሪ ሆኖ፣ ወንድማችንና አጋዣችን ሆኖ፣ መሾሙ ነው፡፡ ተቀድቶ ከማያልቀው የኀይል ገንዳ ጋር በጥልቅ መንፈሳዊ ግንኙነት ተገጣጥመን፡፡ እርሱ ራስ ቢሆን እኛ አካሉ ሆንን፡፡ እርሱ ምንጭ ቢሆን እኛ አሸንዳው ሆንን፡፡ ቤተክርስቲያን የኢየሱስ ኀይል መንዶልዶያ ናት፡፡ ለአፍታ እንኳ መሥመራችን ቢዋልል ድንገተኛ የኀይል መቋረጥ ያጋጥመናል፡፡ እርሱ እንዲህ አለ፡፡ “ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉም”፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ ቦታ በቤተክርስቲያን ሌሎች የገነኑ እንደሆኑ፣ አነዳንድ ደማቅ ጎምላሎች አደባባዩን ያጣበቡ እንደሆነ አሸንዳችን ተሳስቶ ከድፍርስ ውሃ ማጠራቀሚያ ጋር ተያይዟል ማለት ነው፡፡ ኀይልም እየተሰለመለመች ትነጥፋለች፣ ባዶ ሽለላና ቀረርቶ ቦታውን ይተካሉ፡፡ በአስተምህሮአችን በቤተክርስቲያን አስተዳደራችን በዕለት ተዕለት የሕይወት እሰጥ አገባ፣ በሥነ ምግባር ውሳኔአችን በሁሉም ሕይወታዊ እንቅስቃሴ ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታና አለቃ መሆኑን በጥንቃቄ ማረጋገጥ ኀይል እንዳይሟጠጥ የምናደርገው ሁነኛ ርምጃ ነው፡፡ ክበር ክበር ክበር በሉት እርሱን ክበር ክበር ክበር በሉት እርሱን ኢየሱስ ሲነግሥ ያፈስሳል መንፈሱን፡፡ እውነተኛው የቤተክርስቲያን ኀይል የመንፈስ ቅዱስ ኀይል ነው፡፡ የክርስቶስ አካል በወደረኞቿ መካከል በዓለማ ቆማለች፣ ግንባር ለግንባር ተፋጣ፣ ሳንጃ ለሳንጃ ተማዛ፣ ወደሞት የሚነዱትን ለመታደግ በታላቅ ተጋድሎ ላይ አለች፡፡ ጠላቶቿ መንፈሳውያን ናቸው ርኩሳን መንፈሳዊያን ውጊያውም መንፈሳዊ ነው፡፡ ዐውዳሚውን መንፈስ የምትቋቋመውና መከረኞቹን ከእጁ የምታራግፈው በተቃራኒው መንፈስ ጉልበት ብቻ ነው፡፡ “እኔ በእግዚአብሔር መንፈስ አጋንንትን የማወጣ ከሆንሁ እንግዲህ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ደርሳለች” “ሰው አስቀድሞ ኀይለኛውን ሳያስር ወደ ኀይለኛው ቤት ገብቶ ዕቃውን ሊነጥቀው ይችላል?” ያለው በእግዚአብሔር ጣት ይንቀሳቀስ የነበረው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ወገኖቼ ይህችን የምንወዳትን አገራችንን ኢትዮጵያን ልብ ብላችሁ ተመልከቷት፡፡ ሕዝቧ በየጉድባውና በየተራራው በየሸለቆውና በየተረተሩ በሜዳውና በጫካው በእንዴት ያለ የዲያብሎስ እሥራት ተጠፍሮ እንደሚሰቃይ እዩ፡፡ በከተሞቻችን ሕንፃዎች ውስጥ በየደሀው ጎጆ ጓዳ በየቱጃሩ ቪላ በየነጋዴው ሱቅ ውስጥ ስንት የጋኔን ካዳሚ እንደፈላ ተመልከቱ፡፡ ዲያብሎስ የልቡና ዐይናቸውን በጥቅርሻ ሱቲ አጨልሞ እዝነ ልቦናቸውን በባዕድ አምልኮ ዝየራ አደንቁሮ በባቄላ ርጋፊ እያባበሉ እንደሚነዱት በግ ለእርድ የሚነዳቸው ስንት ናቸው? የዛሬዋ ኢትዮጵያ እንዳለችበት ሁኔታ ኀይል ጠሪ ዘመን ይኖር እንደሆነ አላውቅም፡፡ ትልቅ ኀይል ያስፈልገናል፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ብርታት ብቻ ሊፈነቃቅለው ለፈረካክሰው የሚችል ቋጥኝ በሕዝባችን ላይ ተጭኗል፡፡ ኀይል ያስፈልገናል ኀይል ያስፈልገናል ክብርህ እንዲሰራፋ መንግሥትህ እንዲሰፋ ኀይል ያስፈልገናል ጌታ ሆይ… መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር አባቴ እንደሆነ እየነገረኝ በሰማይ ርስት እንዳለኝ እያሳወቀኝ በፍጥረቴ ውስጥ የሌለ ቅዱስ ድፍረት ይሞላኛል በነገር ሊያጠምዱኝ በተሰበሰቡ ተኩላዎች ውስጥ የተንኮል ጥበባቸውን እየገሠሠ እውነትን በግልጠነት እንድናገር አፍ ይሆነኛል፡፡ ይህ የኀይል መንፈስ አንድ ብቸኛ ናፍቆትና ጥሪ ሞልቶ ነፍሴን ለታላቁ ዓላማ እንድትገሠግሥ እግሯን ያረታል፡፡ “መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኀይልን ትቀበላላችሁ” ያለው ጌታ ኢየሱስ ድንጉጥና ብርግግ የነበሩትና ልባቸው ያልተረጋጋውን አሠራ አንድ ወዳጆቹን ነው፡፡ ማንም ምስኪን በእነዚህ ድንጉጦች አብነት በኀያሉ መንፈስ ተሞልቶ ሌላ ሰው ሊሆን ይችላል፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች የሚሰጡን እኮ ለጌጥና ለአንቲክ አይደለም፡፡ “ለስሟ መጥሪያ ቁና ሰፋች” እንደተባለው መለዮ እንድንቀበልበት አይደለም፡፡ ለሥራ ነው ለሥራ፡፡ የሥጋ ክንድ የማይችለውን ብርቱ ሥራ ለመሥራት ነው፡፡ “የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፡፡ ለድሆች ወንጌልን እንድሰብክ እርሱ ቀብቶኛልና ለታሠሩት መፈታትን ለታወሩትም ማየትን እንዳውጅ የተጨቆኑተን ነፃ እንዳወጣ የተወደደችውን የጌታን ዓመት እንዳውጅ ልኮኛል፡፤” ወዳጆች ሆይ ቤተ ክርስቲያን ምንም ታክቲክ ቴክኒክ፣ ብልጠት የላትም፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ኀይል ብቻ ነው ባለድል የሚያደርጋት፡፡ የክርስቶስን መስቀልና ትንሣኤ የሚያውጀው ወንጌል የቤተክርስቲያን ኀይል ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ከወንጌል የረቀቀ ከመስቀሉ ቃል የመጠቀ ፍልስፍና የላትም፣ አያስፈልጋትምም፡፡ ምክንያቱ ግልጥ ነው፡፤ “ከእግዚአብሔር ጥበብ የተነሳ ዓለም በገዛ ጥበቧ እግዚአብሔርን ማወቀው ስለተሳናት በስብከት ሞኝነት የሚምኑትን ለማዳን የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ሆኗል፡፡” በየዘመኑ የሚነሱ ልዩ ልዩ አስተምህሮዎች ጠቃሚነታቸው ያንን አሮጌ ወንጌል ያጸኑ የገለጡ ያጎሉ እንደሆን ብቻ ነው፡፡ በላዩ ላይ በሚከምሩት የፍልስፍና ቅራቅንቦ መልኩን የሰወሩት እንደሆን ወንጀለኞች ናቸው፡፡ ወንጌል ብቻውን መለኮታዊ ኀይል ነውና፡፡ “በወንጌል አላፍርም ምክንያቱም ለሚያምን ሁሉ ለድነት የሚሆን የእግዚአብሔር ኀይል ነው፡፡” ሰው የሚድነው ወንጌለ ክርስቶስ ሲነገረው ነው፡፡ እያደገ እየጎለበተ የሚሄደውም ይኸው የወንጌል እውነት በሠራ አካላቱ ሲዘልቅ ነው፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት ÷ ድል አድራጊ ትንሣኤውና ተመልሶ መምጣቱ የዕድሜ ልክ ትምህርታችን ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሌላ እንቶ ፈንቶ ለማውራት ማን ፈቀደላት? የጽድቅ ሕይወት የቤተክርስቲያን ኀይል ነው፡፡ የወረወርነው ሄዶ ኢላማውን የማይመታው ቢመታውም የማያቆስለው የተናገርነው የማይሠራው ጩኸት ብናበረክትም ዝንብ የማናባርረው ልፋታችን መና የሚቀረው ለምንድነው እያልን የማንጠይቀው ለምንድነው? በክፋትና በርኩሰት በሰለጠነ ዓለም ውስጥ በተመሳሳይ መሣሪያ ልናሸንፍ ስለማንችል ነው፡፡ የሰይፋችንን ስለት ያዶለዶመው ጽድቅ አልባ ሕይወታችን ነው፡፡ ድፍረታችን የሚመነጨው በጌታ ዘንድ ካለን ተቀባይነት የተነሳ እንደሆነ አሌ አይባልም በዚሁ ትይዩ ግን መጽሐፈ ምሳሌ ደግሞ “ጻድቅ እንደ አንበሳ ደፋር ነው” ይለናል፡፡ የክርስቲያኑ ማኅበረሰብና በውስጡ ያሉት አባላት ስለ ንጹህ ሕይወት ያላቸው መጠበብ ምን ያህል ነው? የሥነ ምግባር መለኪያቸው ምንድነው? ስለ ሐሰት ስለ ሐሜት ስለ ሀቅ ሰለ ርኀራኄ ስለ ይቅርታ ስለ ፍቅር ምን እያደረጉ ነው? ምን እያሉ ነው አላልኩም ምን እየሠሩ ነው? ነው ያልኹት፡፡ “ትዕዛዜን ሰምተህ ብቻ ቢሆን ኖሮ ሰላምህ እንደ ወንዝ ጽድቅህ እንደ ባሕር ሞገድ በሆነ ነበር” የባሕር ሞገድን ያህል ጉልበታምና ጉልህ የሚንሰራፋም ጽድቅ ከፈጣሪያችን ጋር በስምረት ከመኖር ይመነጫል፡፡ ያ ንጹሕና ደፋር ኢየሱስ ያስቀናኛል፡፡ አምርረው በሚጠሉትና በከንቱ በሚያሳቅሉት ራስ ፀደቅ ጎምላሎች ፊት “ከእናንተ ስለ ኃጢአት በማስረጃ የሚሰኝ አለን? ብሎ የጠየቀ ግልጥ ሰው ነበር፡፡ ጉልበት ማለት ይህ ነው እኛ እንደዚህ ማለት ችለን ብንሰቀል ስንት ምሕረት በወረደ፡፡ የተባለው ሁሉ ተብሎ የቤተ ክርስቲያን ኀይል የቂምና የበቀል የጥላቻና የቁርሾ የንፍገትና የጠባብነት መርዝ ሳይሆን የፍቅር ኀይል ነው፡፡ ፍቅር ፎልፏላ፤ ነው እጁን ዘርግቶ ባለ አርባ እሾህ ጃርት ያቅፋል፡፡ ደሙ እየፈሰሰ ለደም አፍሳሾቹ ይፀልያል፡፡ ይህን ዓለም የምናድነው መዓት እንዲወርድበት በመፀለይ አይምሰላችሁ የዚህን ዓለም መሠሪዎች የፖለቲካ ጮሌዎችን የመንገድ ዳር ዱርዬዎችን ጎዳና አደር እንስቶችን የልዩ ልዩ ስህተት ኃይማኖት አራማጆችን ለፍቶ አዳሪ ብከኖችን የእጽዋት ሱስ ባሮችን የተማሩ ማይሞችን እውነት ፈላጊ እውሮችን ካልወደድናቸው አናድናቸውም፡፡ ብዙ ሰው ብዙ ብርቱ መሳሪያ ሊቋቋም ይችላል፡፡ ፍቅርን ግን መገፍተር ቀላል አይደለም፡፡ የጨካኞች እንኳ በፍቅር ፊት ይልፈሰፈሳል፡፡ ፍቅር እያለዘበ ድንጋይ እንደሚሰብር ውሃ በለሆሳስ ዘላቂ ሥራ ይሠራል፡፡ የማንወድ ከሆንን ክርስቲያንነት መጠሪያ ብቻ ሆኖብናል፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስ ኀይል የፍቅር ኀይል ነውና፡፡  

Leave a Reply